ባለፉት አምስት ዓመታት የኢትዮጵያን ዕለታዊ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ኢንዱስትሪ በመምራት ረገድ ግንባር ቀደም ሚና ሲጫወት የቆየው አቦል ቴሌቪዥን፤ ዛሬም ይህንን ጉዞ ይበልጥ በማጠናከር አዲስ የታሪክ አሻራ የሚያሳርፍ ስራ ይዞ ቀርቧል። በኢትዮጵያውያን ጸሐፊያን ሙሉ በሙሉ ተፅፎ ለተመልካች የሚቀርበው "በሚስጥር" የተሰኘው ባለ 260 ክፍል ረጅም ቴሌኖቬላ (Long-running Telenovela) ከመጋቢት 22 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ስርጭቱን ይጀምራል።
አቦል ቻናል ከዚህ ቀደም ከ120 በላይ የፕሮዳክሽን ድርጅቶች ጋር በመሆን በርካታ ውስን ተከታታይ (Limited Series) እና መካከለኛ ርዝማኔ ያላቸውን ድራማዎች ሲያቀርብ ቆይቷል። አሁን ግን ይህንን መሪነቱን ይበልጥ በማሳደግ በሶ ሪል (So Real) ፊልም ፕሮዳክሽን ተዘጋጅቶ በኤምኔት ኦሪጅናል (M-Net Originals) ፕሮዲዩስ የተደረገውን ይህን ግዙፍ ስራ ለተመልካች አቅርቧል። ይህ ታላቅ ኢንቨስትመንት አቦል ለሀገራችን የኪነ-ጥበብ እድገት ያለውን ቁርጥኝነትና ለተመልካቾች የሚገባውን የላቀ የመዝናኛ አማራጭ ለመስጠት የሚሄድበትን ርቀት የሚያሳይ ነው።
የ"በሚስጥር" የታሪክ አወቃቀር ከርዝማኔው ባለፈ የእያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ የቤተሰብ ጓዳ የሚፈትሽና እጅግ ተአማኒ ነው።
- ወቅታዊነት፦ የድርሰት ስራው የህብረተሰቡን ባህል፣ ሁነቶች እና በዓላትን ድራማው ከሚተላለፍበት ወቅት ጋር አብሮ እንዲሄድ ተደርጎ የተፃፈ በመሆኑ፣ ተመልካቾች ታሪኩን የራሳቸው የህይወት አካል አድርገው እንዲመለከቱት ያደርጋል።
- መልክአ-ምድራዊ ስብጥር፦ የቀረጻ ስራው በአዲስ አበባ፣ መቂ፣ አርባምንጭ እና ሞጆ ከተሞች የተከናወነ ሲሆን፣ ይህም ለተመልካች የተለያየ መልክአ-ምድርና የላቀ የሲኒማቶግራፊ ጥራት እንዲያገኝ ያስችለዋል።
- ቴክኖሎጂ፦ ዘመኑ የሚጠይቀውን የምስል፣ የድምፅና የመብራት መሳሪያዎችን ከመጠቀም ባለፈ፣ ለድራማው ተብለው የተገነቡ ዘመናዊ ስቱዲዮዎች የኢንዱስትሪውን የአሰራር ጥበብ ወደ ላቀ ደረጃ አሸጋግረውታል።
የተሰጥኦዎች ጥምረት የሚታይበት ድራማው አንጋፋዎችን እና አዳዲስ ኮከቦችን በአንድ መድረክ አገናኝቷል፦
- በ"ፍቅር እስከ መቃብር" ድራማ የብዙዎችን ልብ የገዛችው መስከረም ነጋ፣ በዚህ ድራማ ላይ ከዚህ ቀደም ከታየችባቸው ገጸ-ባህሪያት ለየት ባለ የዘመናዊ ከተማ ሴት ስብዕና ተመልሳለች።
- ወጣት ተዋናይት ትምኒት ገብረኪዳን "ተአምር" በሚለው የዋና ገጸ-ባህሪ ሚና በመሳተፍ አዲስ ተሰጥኦዋን የምታሳይበት እድል ተፈጥሮላታል።
- በተጨማሪም እንደ በፍቃዱ ከበደ፣ አዜብ ወንደሰን፣ ሄለን ሳሙኤል፣ ቴዎድሮስ እሸቱ፣ ቢኒያም መንግስቱ፣ ያሬድ ኃይለሚካኤል እና ልያት ስዩም ያሉ ዝነኛ ባለሙያዎች ተሳትፈውበታል።
የመልቲቾይስ ኢትዮጵያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ገሊላ ገብረሚካኤል "ይህ ታላቅ ኢንቨስትመንት መልቲቾይስ አፍሪካ ለኢትዮጵያ ፈጠራና ለኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ያለውን ጥልቅ እምነት የሚያሳይ ነው። 'በሚስጥር' የተሰኘውን ይህን ኦሪጅናል ድራማ ስናበስር፣ ተመልካቾቻችን የራሳቸውን ማንነት፣ ባህል እና እሴት በላቀ ጥራት እንዲመለከቱ ለማድረግ ያለንን ቁርጠኝነት ዳግም እናረጋግጣለን። በሀገራችን ባለሙያዎች ሙሉ በሙሉ የሚዝጋጁ ኦሪጅናል ታሪኮች የፊልም ኢንዱስትሪያችንን ለማሳደግ ዋንኛ ሞተሮች እንደሆኑ እናምናለን፤ አቦልም ለውድ ተመልካቾቻችን የሚገባውን የላቀ የመዝናኛ አማራጭ ለማቅረብ ሁልጊዜም ዝግጁ ነው።"
ከኪነ-ጥበብ እሴቱ ባለፈ ፕሮጀክቱ ከ45 በላይ ለሚሆኑ ባለሙያዎች ቋሚ ስራ፣ እንዲሁም ከ500 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ጊዜያዊ የስራ ዕድል በመፍጠር የዘርፉን ዕድገት ደግፏል። በተለይም ዋና ጸሐፊውና ፕሮዲዩሰሩ ሶፎንያስ ታደሰ፣ አዳዲስና ጀማሪ ጸሐፊያንና ዳይሬክተሮች በስራው ላይ እንዲሰለጥኑና እንዲሳተፉ በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል።
የስርጭት መርሃ-ግብር
- የሚጀምርበት ቀን፦ መጋቢት 22 ቀን 2018 ዓ.ም (March 31, 2026)
- ቀናት፦ ከሰኞ እስከ ዓርብ
- ሰዓት፦ ምሽት 2፡00 ሰዓት (8:00 PM)
- ቻናል፦ ጎጆ ጃኬጅ አቦል ቴሌቪዥን (DStv ቻናል 465) ብቻ
በ #MyDStv መተግበሪያ አሁን አገልግሎቱን ያስቀጥሉ: https://mydstv-thiane.onelink.me/ivCe/qpuy2sa6
በ DStv Stream መተግበሪያ የሚወዱትን ድራማዎች ይከታተሉ!
