channel logo
Girid Showpage Billboard
channel logo

Girid

465DramaPG13

ግርድ ድራማ - እስከ አሁን ምን ምን ተከሰተ?

ዜና07 ኦክቶበር 2025
ግርድ ድራማ ከአራት ክፍሎች በኋላ ተወሳሰቦ የቆየ ክህደት፣ አዳዲስ ግጭቶች እና የተደበቁ እውነቶች ወዳሉበት ዓለም ወስዶናል።
Girid Article poster

ግርድ ድራማ ከአራት ክፍሎች በኋላ ተወሳሰቦ የቆየ ክህደት፣ አዳዲስ ግጭቶች እና የተደበቁ እውነቶች ወዳሉበት ዓለም ወስዶናል። ከሃያ ዓመታት በፊት በተካሄደ ሚስጥራዊ የመንግስት የምርምር ፕሮጀክት ዙሪያ የተፈጠሩ ክስትቶችና መዘዛቸው ላይ የሚያተኩረው ታሪኩ ገና መገለጥ እየጀመረ ነው።

እስከ አሁን የተመለከትናቸው ዋና ዋና እና ውጥረት የበዛባቸው ክስተቶች እነሆ፦

የሚንገዳገድ ቤተሰብ እና ጨካኝ መሪ

ከሚስጥራዊው ፕሮጀክት የመጀመሪያ አባላት አንዱ የሆነው ዘሪሁን፣ በልጁ ያሬድ አስቸጋሪ ባህርይ ምክንያት ከሚስቱ አስቴር ጋር ያለማቋረጥ ይጣላል። የቤተሰብ ውጥረት ቢኖርበትም፣ ዘሪሁን በአደባባይ ያለውን ጨካኝ ገጽታውን ጠብቆ ቆይቷል። ይህም አሁን ላይ በሚሰራው ፕሮጀክት ዙርያ ድክመቱን የሚያጋልጥ ዜና ያወጣችውን ጋዜጠኛ ዘገባውን እንድታነሳ በማስፈራት የማስተባበያ ዘገባ ሲያሰራት ይስተዋላል። ዘሪሁን ለሃያ ዓመታት ያህል ተገሏል ብሎ ያስበው የቀድሞ ጓደኛው አቤል በሕይወት እንዳለና ፍትህን እየፈለገ መሆኑን ሲያውቅ፣ ህይወቱ ይበልጥ የተወሳሰበ ሊሆን ነው።

የጽዮን የልደት ቀን

የግጭቱ ማዕከል እንደሆነች የማታውቀው ወጣት ጽዮን፣ ለልደቷ ቀን የተላኩላት ስም አልባ ስጦታዎች በጣም ግራ አጋብተዋት ነበር። የቅርብ ጓደኛዋ ብርሃኑ ግን ወደ ቤቷ በመሄድ ቀኗን አበራው፣ ቀጥሎም ሁለቱ በአንድ ላይ የልደት ቀኗን አክብረዋል።

በፓርቲው የተፈጠረው ግጭት

ግን ደስታው ብዙም ሳይቆይ ቀረ። ብርሃኑ እና የጽዮን የቀድሞ ፍቅረኛ የሆነው ያሬድ (የዘሪሁን ልጅ)፣ ለግቢው ተማሪዎች በተዘጋጀው ፓርቲ ላይ ከፍተኛ ግጭት ውስጥ ገቡ። ግጭቱ ሲካረር፣ ያሬድ ብርሃኑን ገፋው። ብርሃኑም ደረጃ ላይ ጭንቅላቱን መትቶ በመውደቁ ወዲያውኑ ወደ ሆስፒታል ተወሰደ።

መመለስ እና መጋለጥ

በድርጊቱ በሚመጣው መዘዝ የፈራው ያሬድ ወደ ቤቱ ሲሮጥ፣ የዘሪሁን የችግር ፈጣሪ ልጅ እንደሆነ ተገለጠልን። ያሬድ እና እናቱም ብርሃኑን ወደተሻለ ሆስፒታል እንዲዘዋወር ረድተዋል።ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ከሃያ ዓመት በፊት የምርምሩ አባል የነበረችው እና ታሪኩ ላይ ትልቅ ሚና ያላት ሳባ ከውጭ ተመልሳለች። ሌላው የፕሮጀክቱ አባልና ዋና መሪ የነበረው አፈወርቅም እንዲሁ ከአቤል የቀድሞ ሥራ ጋር በተያያዘ ጉዳይ ከውጭ ተመልሷል።

በሆስፒታሉ የተፈጠረው ገጠመኝ

ብርሃኑ ራሱን ስቶ (ኮማ ውስጥ) ሆኖ ውጥረቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል። ጽዮን በብርሃኑ ስልክ ላይ ያገኘችውን የቤተሰብ ስልክ ቁጥር ስትደውል፣ የአቤል ስልክ ሆኖ አገኘችው። ብርሃኑ ሆስፒታል እንደገባ ሲሰማ፣ አቤል ለሃያ ዓመታት ተደብቆበት ከነበረው ገጠራማ አካባቢ ወደ ከተማ ተመለሰ።

ዘሪሁንም እንዲሁ በልጁ ድርጊት የተፈጠረውን ችግር ሲያውቅ ወደ ሆስፒታል ሄደ። እዚያም፣ አቤል እና ዘሪሁን ከሃያ ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ፊት ለፊት ተገናኙ!

ከክስተቱ በኋላ

ዘሪሁን አቤልን በህይወት በማየቱ ደንግጧል፣ በልጁ እና በሚስቱ ደግሞ ተናድዷል። ምንም እንኳን አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑም፣ አቤል፣ ጽዮን እና ያሬድ ብርሃኑ ከኮማው እስኪነቃ ድረስ በሆስፒታል ውስጥ እየጠበቁ ናቸው።

ወደ ቀደመው ዘመን መስኮት

በእነዚህ አሁን ባሉ ግጭቶች መካከል፣ ከሃያ ዓመታት በፊት ስለተፈጠረው ክህደት እና አቤል እንዲጠፋ ስላደረጉት ክስተቶች የሚያሳዩ አጫጭር ትውስታዎችን እያየን ቆይተናል።

ይህ ሁሉ ሚስጥር ሳይገለጥ፣ በቀል ፈላጊው አቤል ወደ ከተማ ተመልሶ፣ የብርሃኑ ዕጣ ፈንታ እርግጠኛ ሳይሆን፣ ታሪኩ ልብ አንጠልጣይና አጓጊ ቅርጽ እንደያዘ ነው! በቀጣይ ክፍሎች ምን ይፈጠራል?

ግርድ”ን ዘወትር ማክሰኞ በአቦል ቲቪዲኤስቲቪ ቻናል 465 ይከታተሉ።

የአቦል ድራማዎች እንዳያመልጥዎ ደምበኝነትዎን ያስቀጥሉ፡ https://mydstv-thiane.onelink.me/ivCe/qpuy2sa6