የካቲት 21፣ 2014 አዲስ አበባ፡ የየካቲት ወር አቦል ቲቪ የተጀመረበትን አንደኛ ዓመቱን የሚያከብርበት ወር ነው፡፡ በዚህም አንድ ዓመት ውስጥ አቦል በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችና ለኢትዮጵያውያን ተመልካቾች የተሰሩ በርካታ ታሪኮችን በማቅረቡ ታላቅ ኩራት ይሰማዋል፡፡
ይህንንም ልምድ ለማስቀጠል፤ ቻናሉ የባስሊቆስ እንባ፣ ጥላ እና ሁለት ጉልቻ የተሰኙ ሶስት አዳዲስ ተከታታይ ድራማዎችን በዚህ ወር ውስጥ ለተመልካቾቹ ለማቅረብ ጉድ ጉድ እያለ ነው፡፡አደይ የተሰኘው ተወዳጁ ቴሌኖቬላም በአዲስ የምዕራፍ ዘመን የሚመለስ ሲሆን በይዘቱ ልዩ የሆነው ሙዚቃዊ ተከታታይ ድራማ ናፍቆትም ተመልካችን ይበልጥ እየሳበ ይቀጥላል።
እ.ኤ.አ. ማርች 8 ቀን 2021 የጀመረው አቦል ቲቪ (ዲኤስቲቪ ቻናል 146) በተለያዩ ዘውጎች እና አተራረኮች የተሰሩ ኢትዮጵያዊ ድራማዎች እና ፕሮግራሞች መገኛ ሆኗል። በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥም በተለይም በጥራትና በጥልቀት የተሰሩ ፕሮግራሞችን ማየት በሚፈልጉ ተመልካቾች ዘንድ ተመራጭ እና ተወዳጅ ቻናል ሆኗል፡፡
“ቻናሉን ስንጀምር ለተመልካቾቻችን ምርጥ ምርጥ የሆኑ ፕሮግራሞችን እንደምናቀርብላቸው ቃል ገብተንላቸው ነበር፡፡ ተመልካቾቻችንም እነዚህን ስራዎቻችንን በጋለ ስሜት ተቀብለው በመመልከት ላደረጉልን ድጋፍ እናመሰግናለን” ትላለች የቻናሉ ኃላፊ ሰርካዲስ መጋቢያው፡፡
እንግዲህ አቦል ቲቪ በዚህ የአንደኛ ዓመት ልደቱ መከበርያ ወር ውስጥ እጅግ በጣም አጓጊ እና አኩሪ የሆኑ አዳዲስ ድራማዎችን ይዞ ቀርቦዋል! የፊታችን አርብ በ2፡30 ላይ የሚጀምረው የመጀመሪያው አቅርቦቱ ‘ሁለት ጉልቻ’ ሲሆን፤ በዚህም ድራማ ላይ ከተለያዩ ሴቶች ጋር የፍቅር ግንኙነት የጀመረን ጎልማሳ ውጣ ውረድና ሴቶቹም እርስ በእርሳቸው ከመዋጋት ይልቅ በህብረት ተባብረው ለጋራ ጠላታቸው ምላሽ የሚሰጡባቸውን ትዕይንቶች እናያለን፡፡
በቀጣዩ ሰኞም በ2፡30 ላይ ጥላ የተሰኘውን ድራማ እናገኛለን። ይህ አስገራሚ ድራማ ደግሞ አንድ ጫካ የተባለ ሰው፣ ገንዘብና ንብረትለማካበት ሲል የወሰደው ውሳኔ በቤተሰቡ ላይ የሚያመጣውን ብዙ ውጣ ውረድ እናያለን፡፡ በዚህ ድራማ ላይ እጅግ ታዋቂዎቹ ተዋንያን መርሻ ጌታሁን፣ አለምፀሐይ በቀለ፣ ሚካኤል ሚሊዮን እና መአዛ ታከለ ተሳትፈውበታል።
ሶስተኛው የአቦል ቲቪ ምርጥና አዲስ አቅርቦት ደግሞ ከመጋቢት ወር መጨረሽዐ ጀምሮ ዘወትር ረቡዕ በ3፡00 የሚተላለፈው ‘የባስሊቆስ እንባ’ የተሰኘው ድራማ ነው፡፡ ይህ ድራማም በትልቅ ከተማ ውስጥ የኮሌጅ ትምህርትዋን የምትከታተል አንዲት ወጣት ተማሪ ለእረፍት ወደ ትውልድ መንደሯ በተመለሰችበት ወቅት የሚገጥሙዋትን ግራ አጋቢ ገጠመኞች ይተርካል። ወጣትዋ ወደ መንደሩ ተመልሳ ከእናቷ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማስተካከልና ከልጅነት ፍቅረኛዋ ጋር የነበራትን ግንኙነት ለመቀጠል ትሞክራለች። ያንን በምትሞክርበት ጊዜም ማንነትዋን ፈልጋ ታገኛለች፡፡
ከእነዚህ ድራማዎችም በመቀጠል ባለፈው ዓመት በታዩት ምዕራፎቹ ተወዳጅነትን ያተረፈው ቴሌኖቬላ ‘አደይ’ በአዲስ ምዕራፍ ይቀጥላል፡፡ (ከሰኞ እስከ አርብ በ2፡00 ሰዓት)። የአደይ ተከታታዮችስ በዚህ ምዕራፍ ምን ይጠብቁ? ብዙ ነገር! በዚህ ምዕራፍ ላይ በአደይና በአቤል ሰርግ ላይ በተነሳው ድንገተኛ የእሳት ቃጠሎ የተነሳ የአቤል ባህሪይ ፍፁም ይቀየራል፡፡ አደይም ከምታስበው በላይ ነገሮች ይለዋወጣሉ፡፡ ቀጥሎም ከአፈና ሴራ ጀምሮ የአምዴን ቤተሰብ የሚያንቀጠቅጡ ብዙ ሁነቶች ይፈጠራሉ፡፡ አንዳቸውም እንዳያመልጡዋችሁ! ከዚህም በተረፈ በቻናሉ ላይ ካሉት ረጅም እና ተወዳጅ ድራማዎች ውስጥ አንዱ የሆነው ሙዚቃዊ ድራማው ‘ናፊቆት’ም በየሳምንቱ ማክሰኞ ከምሽቱ 2፡30 ላይ ለተመልካቾች መቅረብ ይቀጥላል።
መልካም ልደት አቦል ቲቪ! ለቀጣዩም አመታት አብሮ በሰላም ያድርሰን! ቻናሉን በአጭር ጊዜ ውስጥ እጅግ ተወዳጅ እና ተመራጭ እንዲሆን የረዳችሁት እናንተ ውድ ተመልካቾቻችንን ናችሁ እና እናንተንም ከልብ እናመሰግናለን!