በዲኤስቲቪ ቻናል 146 ላይ የሚተላለፈው አቦል ቲቪ እስካሁን በጣም ተወዳጅና አጉዋጊ ሆኖ የዘለቀውንና ‘አደይ’ የተሰኘውን የቴሌቭዥን ተከታታይ ድራማ ምእራፍ 2 ሰኔ 21 2013 ከምሽቱ 2 ሰዓት ላይ ለመጀመር ዝግጅቱን አጠናቅቁዋል፡፡
የአቦል ቴሌቭዥን ስራ አስኪያጅ ሰርካዲስ መጋብያው፦ “አደይ ምዕራፍ 1 በተመልካቾቻችን ዘንድ ትልቅ ተቀባይነት ያገኘ ድራማ ነው ፡፡ አዲሱን ምዕራፍ ደግሞ ይበልጥ ከፍ ባለ የታሪክ ፍሰት ቀጥለን ተመልካቾቻችን ዓይኖቻቸውን ከቴሌቭዥናቸው ላይ ሳይነቅሉ ከሰኞ እስከ አርብ ያለውን ምሽታቸውን ከእኛ ቻናል ጋር እንዲያሳልፉ ለማድረግ ዝግጁ ነን” ብላለች፡፡ ሁሉም ሰው ድራማውን ልክ እንደ መጀመሪያው ምዕራፍ በጋለ ስሜት እንደሚቀበለውም ተስፋ እንዳላት ገልፃለች ፡፡
እንግዲህ የመጀመሪያው ምዕራፍ ንፁህዋ አደይ እስር ቤት ውስጥ ታስራ ተጠናቅቋል ፡፡ አደይ በጣም የምትወድደውና ጥፋተኛ እንዳልሆነች የሚያምነው አቤል ያድናት ይሆን? ወይዘሮ ሮማን እና ራሔልስ ለእርዳታ እጃቸውን ይዘረጉላታል? ከሳሾችዋስ በእሷ ላይ ሌላ ምን ሴራ ይጎነጉኑ ይሆን? ይህ የታሪክ ጥልፍልፍ እንዴት እንደሚፈታ አብረን የምናየው ይሆናል።
በአቦል ቲቪ ላይ ሌላ የሚታዩ ድራማዎች :
ዙረት ሰኞ ከምሽቱ 2፡30
ናፍቆት ማክሰኞ ከምሽቱ 2:30
አስኳላ ረቡዕ ከምሽቱ 1፡30
ጎጇችን አርብ ከምሽቱ 2፡30
ስለ አደይ
አደይ በአንዲት የ17 ዓመት ልጃገረድ የህይወት መንገድ ላይ የተገናኙትን ሁለት የተለያዩ ቤተሰቦች የሕይወት ጉዞ ውስጥ የሚፈራረቁትን በርካታ የሕይወት ገጽታዎችን የሚያሳይ ሳምንታዊ ድራማ ነው ፡፡ ድራማው በቤተሰብ ፣ በወዳጅነት ፣ በእውነት ፣ በታማኝነት ፣ በሀገር በቀል ዕውቀት ፣ በሥነ ጥበብ እና ከሁሉም በላይ ደግሞ በፍቅር ላይ የተመሰረቱት ታሪኮችን በውስጡ ያሳያል ፡፡
ስለ አቦል ቲቪ
አቦል ቲቪ ፣ በቅርቡ በዲኤስቲቪ ቻናል 146 ላይ ስራ የጀመረና ለኢትዮጵያውያን የቀረበ የመዝናኛ ጣቢያ ነው ፡፡ ጣብያው በኢትዮጵያዊ ባለሙያዎች ተዘጋጅተው፤ ለአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ቤተሰብ የሚመጥኑ፤ ሀገርኛ ይዘት ያላቸውና ከእያንዳንዱ ተመልካች ህይወት ጋር ሊዛመዱ የሚችሉ ፕሮግራሞችን በመተረክ ይታወቃል፡፡