Logo
Afaf S1

አቦል ቴሌቪዥን ግዙፉን ልብ አንጠልጣይ “አፋፍ” ቴሌኖቬላ ለተመልካቾች ሊያደርስ ነው

ዜና
31 ሜይ 2023
ጋዜጣዊ መግለጫ
Afaf S1 press release

አዲስ አበባ፡ ከኢትዮጵያውያን ዕውቅ የፊልም ባለሙያዎች ጋር በድንቅ ጥምረት ስራዎችን የሚሰራው አቦል ቴሌቪዥን ለተመልካቾች እጅግ አስደሳችና ለደንበኞች የሚመጥኑ አዳዲስ ይዘቶችን እያቀረበ ነው፡፡

አፋፍ ግዙፍ፣ በኢትዮጵያ የቴሌቪዥን ተከታታይ ድራማዎች ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ራሱን የቻለ የቀረፃ መንደር በመገንባት ፕሮዳክሽኑን እያከናወነ የሚገኝ ልብ አንጠልጣይ ቴሌኖቬላ ነው፡፡

የአፋፍ ታሪክ የሚጀምረው ዙማ በተባለ የምናብ መንደር ውስጥ ባለ ግዙፍ ተራራ ላይ ነው፡፡ ታሪኩ የሚጀምረው በ1984 ዓ.ም የዙማ መንደርን የመቀየር ህልም በታጠቁ ሁለት ጓደኛሞች ታሪክ ዙሪያ በማጠንጠን ነው፡፡ ሁለቱ ወጣቶቹ ከእለታት በአንዱ ቀን ሰው ዝር በማይልበት ግዙፉ ተራራ ዙሪያ ሲሯሯጡ ድንገት አንድ በጣም ውድ ማዕድን ይገናኛሉ፡፡ ይህም የማዕድን ግኝት በእነዚህ ሁለቱ ጓደኞችና በዙሪያቸው ባሉ ሰዎች ዙሪያ ያለውን ድህነት፣ ህልም፣ ምስጢር፣ ክህደት፣ ጭካኔ፣ ስግብግብነትና ተቃርኖ እያሳየ ልብ ሰቅዞ በድንቅ ትወና፣ በአስገራሚ ፕሮዳክሽንና በልብ አንጠልጣይ የታሪክ ፍሰት ታግዞ ይቀጥላል፡፡

አፋፍ ቴሌኖቬላ “ዘ ሪቨር” ከተሰኘው የኤምኔት ተወዳጅ የደቡብ አፍሪካ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ታሪክ በመነሳት የኢትዮጵያን ወግ፣ ባህል፣ እሴትና የአኗኗር ይትባሃል በጠበቀ ሁኔታ የተዘጋጀ ድራማ ነው፡፡ ‘’አፋፍ’ በታዋቂው አርቲስት ሚካኤል ሚሊዮን ፕሮዲዩስ የተደረገ ሲሆን በቴሌቪዥን ድራማዎች ትወና አንቱታን ያተረፉት መዐዛ ታከለ፣ ነብዩ ባዬ፣ አለምሰገድ አሰፋ እና ሌሎች በማራኪ ትወናቸው ገፀ-ባህሪያትን ሆነው የሚተውኑበትና በአቦል ቴሌቪዥን ለረጅም ጊዜያት በየዕለቱ ከሰኞ እስከ አርብ የሚተላለፍ ቴሌኖቬላ ነው፡፡

የመልቲቾይስ ኢትዮጵያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ገሊላ ገ/ሚካኤል “የአፋፍን ቅድመ የፕሮዳክሽን ሂደት በቀረጻ መንደሩ ተገኝተን ጎብኝተናል፡፡ በጥብቅ ስነ-ምግባር፣ በከፍተኛ ዝግጅትና በላቀ የፕሮዳክሽን ጥራት ለተመልካቾች እንዲደርስ በትጋት የተሰራ ነው፡እኛ ለተመልካቾቻችን ሁልጊዜም የላቁ የመዝናኛ ይዘቶች እንዲቀርቡ ጥረት እያደረግን ነው፡፡ የይዘቱ ባለቤት ኤምኔትም ለኢትዮጵያውያን ተመልካቾች ዘወትር የላቁ ቴሌኖቬላዎች እንዲዘጋጁ እያደረገ ይገኛል፡፡ ይህ ቴሌኖቬላም በከፍተኛ ወጪና ዝግጅት እየተሰራ ያለና ለኢትዮጵያ ፊልም ዕድገት የራሱን አሻራ ማኖር የሚችል እንደሚሆን እተማመናለሁ፤ ስርጭቱ ሲጀመር በእርግጠኛነት አፋፍ መነጋገሪያና አርዓያ የሚሆን ቴሌኖቬላ መሆኑ አይቀሬ ነው” ብለዋል፡፡

ማኔጂንግ ዳይሬክተሯ አክለውም “የእኛ ለሀገር በቀል ይዘቶች መጎልበት የስትራቴጂ አካል እንደመሆናችን መጠን በአገር ውስጥ መዝናኛዎች ለደንበኞቻችን ምርጥ ምርጡን ለማቅረብ ቆርጠን ተነስተናል። ዓላማችን ተመልካቾቻችንን የሚማርኩና ከዕለት ከዕለት ህይወታቸው ጋር ቀረቤታ ያላቸውን አሳማኝ ታሪኮችን በላቀ ጥራት ማቅረብ ነው። የፕሮዳክሽን ቡድኑ አባላትም ሆኑ የአቦል ቴሌቪዥን ተመልካቾች አስደሳችና ልዩ የመዝናኛ ጊዜን ከአፋፍ ቴሌኖቬላ ጋር እንደሚያጣጥሙ እምነታችን የጸና ነው’ ብለዋል፡፡

አፋፍ ሰኔ 19 ቀን 2015 ዓ.ም (ጁን 26 ቀን 2023 እኤአ) መተላለፍ የሚጀምር ሲሆን ዘወትር ከሰኞ እስከ አርብ ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት ጀምሮ የሚቀርብና ተመልካቾች አንድ ቀንም ሊያመልጣቸው የማይገባ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ነው፡፡